አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10 ቀን 2019 ዓ.ም፡- የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብና የኦዲት ጥራት ማሻሻልን በተመለከተ የግምገማ ግኝቶችና የማሻሻያ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ።
በውይይቱ ላይ የቦርዱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሀገር ኢኮኖሚ እድገትና የሕዝብ ጥቅም ላይ ያላቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቁ የፋይናንስ መግለጫዎችን ማዘጋጀትና ድርጅቶችን ከውድቀት ሥጋት መከላከል ወሳኝ መሆኑን በመድረኩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ገልጸዋል።
በተመሳሳይ፣ የፋይናንስ ሪፖርት ግምገማ አማካሪው አቶ ፍቅሩ ፋንታሁን ድርጅቶቹ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በመንግሥት ገቢ ማሳደግ፣ የግሉን ዘርፍ ማበረታታትና ብሔራዊ ሀብትን በኃላፊነት ማስተዳደር ያላቸውን ሚና በማንሳት፣ በግምገማ የተለዩ ግኝቶችና የማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች መተግበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የኦዲት ጥራት ግምገማ አማካሪው አቶ አበራ ዘውዱ በበኩላቸው፣ የድርጅቶች አመራሮች፣ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ኦዲተሮችና ተቆጣጣሪ አካላት የየራሳቸውን ኃላፊነት በተገቢው መወጣትና የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት ለኦዲት ጥራት መሻሻል ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።
በመድረኩ በተደረገው ውይይትም የተሻሉ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ መድረክ ማመቻቸት፣ ኢንዱስትሪ-ተኮር የኦዲት ባለሙያዎችን ማፍራትና የሕግ ማዕቀፎች ሲዘጋጁ ቦርዱን ማሳተፍ የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ሆነው ተነስተዋል።





