አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8 ቀን 2019 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ (AABE) ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃን (Full IFRS) በሚተገብሩ ተቋማት ላይ ሲያከናውን የቆየውን የፋይናንስ ሪፖርት ግምገማ (Financial Report Review – FRR) ቁልፍ ግኝቶችና የቁጥጥር ማሻሻያ እርምጃዎችን የተመለከተ የምክክር መድረክ በግራንድ ኤሊያና ሆቴል አካሄደ።
በመድረኩ የባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች (CEOs) እና የፋይናንስ ኃላፊዎች (CFOs) ተሳትፈዋል።
የፋይናንስ ሪፖርቶች ጥራትና ተዓማኒነት መጠናከር ለባለሀብቶች፣ ለተቆጣጣሪ አካላትና ለሌሎች የፋይናንስ መረጃ ተጠቃሚዎች ትክክለኛና ተዓማኒ ውሳኔ ለመውሰድ ወሳኝ መሠረት ከመሆኑም ባሻገር የሀገሪቱን የፋይናንስ ሪፖርት ሥርዓትና የቁጥጥር ማዕቀፍ ለማጠናከር ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን በመግለጽ፤ የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ በግምገማው የተገኙ ግኝቶችን ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በመወያየት የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ጥራትን ማሻሻል፣ የኦዲት ጥራት ቁጥጥርን ማጠናከር እና በተቋማት መካከል የጋራ ግንዛቤና ትብብርን ማሳደግ መሆኑን የቦርዱ ም/ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍቃዱ አጎናፍር መድረኩን በከፈቱበት ወቅት ተናግረዋል።

በውይይቱ የፋይናንስ ሪፖርት ግምገማ ወቅት የተለዩ ቁልፍ ግኝቶች፣ እንዲሁም የፋይናንስ መረጃዎችን ግልጽነት፣ ተዓማኒነትና ጥራት ለማሳደግ ሊወሰዱ በሚገቡ እርምጃዎች ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል።
በመድረኩ የፋይናንስ ሪፖርት ግምገማ ግኝቶችን በተመለከተ በአቶ ሰሎሞን ቂጣታ ፣ የፋይናንሺያል ሪፖርት አማካሪ፣ እንዲሁም የሪፖርት አቀራረብንና የኦዲት ጥራት ቁጥጥርን ለማጠናከር በተደረጉ የቁጥጥር ማሻሻያዎች ላይ በአቶ በርናባስ ጌቱ፣ የኦዲት ጥራት ማረጋገጥ አማካሪ፣ ገለጻዎች ቀርበዋል።
ከገለጻዎቹ በኋላ በተካሄደው የጥያቄና መልስ እነዲሁም የውይይት መርሐ ግብር ተሳታፊዎች በተለዩት ግኝቶችና በቀረቡት የማሻሻያ እርምጃዎች ላይ ምክረ ሐሳቦቻቸውን አቅርበዋል።
በቀጣዮቹ ተከታታይ ሶስት ቀናት ከማይክሮ ፋይናንሶች፣ከመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ከሌሎች ሙሉ ለሙሉ አይኤፍአርኤስን /IFRS/ ከሚተገብሩ ተቋማት ጋር ውይይቱ የሚቀጥል ይሆናል።


