የኢትዮጵያ የሒሣብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በ51 የኦዲት ድርጀቶች ላይ የኦዲት ጥራት ምርመራ ለማካሄድ ባቀደው መሠረት እየሠራ መሆኑን አስመልክቶ ባጋጠሙት የአፈፃፀም ተግዳሮቶች ላይ ከሚመለከታቸው የኦዲት ድርጀቶች አመራሮች ጋር ተወያየ፡፡
በውይይቱም የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ለድርጅቶቹ አመራሮች እንደተናገሩት ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ እየተከናወነ ያለው የኦዲት ጥራት ምርመራ ሙያ የበቂ እና ብቁ ባለሙያ እጥረት፣ የኦዲት ድርጅቶች ለሙያው አስፈላጊው ትብብር አለማሳየት፣ መማማር ላይ ከማተኮር ያለፈ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ አለመወሰድ እና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች ምክንያት በሚጠበቀው መጠን ዓላማውን ማሳካት ላይ ውሱንነቶች መታየታቸውን ገልፀዋል፡፡
የኦዲት ድርጅቶቹ አመራሮችም ክፍተቱ ለሙያው ያለመተባበር ሳይሆን በተለያዩ ተፈጥሮአዊ እና ወቅታዊ ተግዳሮቶች ምክንያት ከቦርዱ ባለሙያዎች ፕሮግራም ጋር አለመጣጣም መሆኑን ገልፀው በቀጣይ በጋራ በመስራት ለማሳካት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ ፍቃዱ ለሙያው ጥራት ዕድገት የባለሙያው አስተዋፅዖ ጉልህ መሆኑን በማውሳት ቦርዱ የጥራት ምርመራ ሥራው በወቅቱ እንዳይተገበር ድርጅቶቹ በተለያዩ ምክንያቶች ቀናቱን በመግፋት ባጋጠሙት ተግዳሮቶች ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ፋንታ መማማር ላይ ያተኮረ ቢሆንም በቀጣይ ባለሙያው ሙያዊ የሥነ-ምግባር ደንቡን እና የቦርዱን ህጎች አክብሮ መሥራት እንዳለበት በመጠቆም እና የጋራ መፍትሔ መሻት እንደሚገባ አብራርተው በቀሪ ጊዜያት ዕቅዱን ለማሳካት ሁሉም ሙያዊ ሚናውን መወጣት ይጠበቃል ብለዋል፡፡