ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የህዝብ ውይይት ተካሄደ
የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ጥር 09 ቀን 2017 ዓ.ም. በምክር ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ የህዝብ ውይይት አካሄደ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ አዋጅ 847/2006 በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት እና የኦዲት ደረጃዎች እንዲተገበሩ በደነገገበት ወቅት ይህንን ለማስፈፀም በቂ እና ብቁ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ማፍራት የሚያስችል ተቋም እንደሚመሰረት ቢገለፅም ይህ ሳይከናወን መቆየቱ ሀገር ከሙያው ማግኘት የነበረባትን ጥቅም ማሳጠቱን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በመድረኩ መክፈቻ ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ መቋቋም የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ለማፍራት እና ሙያውን ለማሳደግ ፤ የሒሳብ ሙያን እና የሒሳብ ባለሙያን በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ መወከል በማስፈለጉ፤ የሕዝብ ጥቅምን የሚያስጠብቅ የሒሳብ ሙያን እና የሙያተኛውን አቅም ማሳደግ በማስፈለጉ ነው ፡፡
በተመሳሳይም ኢንስቲትዩቱ የሒሳብ ሙያን ማሳደግ እና ቀጣይነቱን ማረጋገጥ፤ የሒሳብ ሙያ የህዝብ ጥቅምን ማስጠበቁን ማረጋገጥ፤ የሒሳብ ባለሙያዎች የላቀ እውቀት፣ ክህሎት፣ ሥነ-ምግባር እና የአሠራር ደረጃ እንዲኖራቸው በማድረግ የሒሳብ ሙያ በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት እና ዕውቅና እንዲያገኝ ማድረግ፤ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የሚኖራቸው ብቁ እና በቂ የሒሳብ ባለሙያዎችን ማፍራት እና የሒሳብ ባለሙያዎችን የሙያ ነፃነት ማስከበር ነው፡፡
በዚህም መሰረት ተወያዩች ኢንስቲትዩቱ መቋቋም ላይ ሙሉ ስምምነታቸውን ያሳዩ ሲሆን ማስተካከያ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ገንቢ ግብዓቶችን አበርክተዋል፡፡