የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ የሒሳብ እና የኦዲት ባለሙያዎች ፍቃድ አሰጣጥ እና የሒሳብ ሙያ ማኅበራት ምዝገባ መመሪያ ቁጥር 805/2013ን ለማሻሻል በወጣ ረቂቅ መመሪያ ላይ በአስተዳደር ሥነስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 መሠረት ታህሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ከባለድርሻ አካላት ጋር ይፋዊ ውይይት አደረገ፡፡

ውይይቱን ማካሄድ ያስፈለገው ላለፉት አራት ዓመታት በመመሪያው አፈጻጸም ወቅት ለታዩ ክፍተቶች መፍትሔ ለማበጀት እና በመመሪያው ውስጥ ያልተሸፈኑ አዳዲስ የአገልግሎት ዓይነቶችን ማካተት በማስፈለጉ እንዲሁም የሒሳብ እና የኦዲት ሙያ በየጊዜው እየሰፋ እና እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ወቅቱን በሚመጥን ባለሙያ ሙያዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል መሆኑን የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ተናግረዋል፡፡

በዕለቱም ከባለድርሻ አካላት መመሪያውን የሚያጎለብቱ ግብዓቶች የተሰበሰቡ ሲሆን በተለይ የሀገራችን ኢኮኖሚ ለዓለም ገበያ እየተከፈተ ባለበት ወቅት የገበያውን ፍላጎት ማሟላት የሚችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እና ባለሙያውም ብቁ እና ተወዳዳሪ በመሆን አቅሙን በማሳደግ ሙያው የህዝብን እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚኖረውን ጉልህ ሚና ለመወጣት በሙያዊ ሥነ-ምግባር የታጀበ ግዴታውን መወጣት እንደሚገባ በውይይቱ ተነስቷል፡፡