የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረውን የተቋማዊ ሪፎርም እንቅስቃሴ እውን ለማድረግ ሐምሌ 04 ቀን 2016 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ለሁሉም ሰራተኖች የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብር አከናወነ፡፡ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጽዋዬ ጥሩነህ እንደተናገሩት ቦርዱ ሁለንተናዊ ለውጥ በማድረግ አሰራሩን ለማሻሻል ጥናት እያደረገ ባለበት ወቅት መንግስት ተቋማት ዓለማቀፋዊ እና ሀገራዊ አሁናዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት የማሻሻያ ሥራዎቹን እንዲሰሩ አቅጣጫ ማውረዱ ለቦርዱ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ `
በዕለቱም በኢፌድሪ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመንግስት ሠራተኞች ብቃት ሥራ አመራር ፕሮጀክት ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አጥሬ እና ወ/ሮ ስርጉት ሚሸል የመንግስት ሠራተኞች ብቃት ሥራ አመራር ፕሮጀክት ከ/ባለሙያ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ከ115 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው ቢሆንም የእድሜውን ያክል ውጤታማ ያልነበረ፣ አሰራሩ ነፃ እና ገለልተኛ አለመሆኑን፣ የሚያረካ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት እንዳልነበረው፣ ብቁ የሰው ኃይል እጥረት የበቁ ተቋማት አለመበራከት፣ የተቋማዊ ለውጥ አመራር እጥረት እንዲሁም
ለፖሊሲ ውሳኔ አጋዥ የሚሆን የተደራሽ መረጃ ሥርዓት አለመኖር ሪፎርሙን ተግባራዊ ለማድረግ ዋነኛ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት ብቁ እና የተገልጋዩን እርካታ ማሳደግ ካለባቸው ሁለንተናዊ ጥናት በማድረግ የሰው ኃይል ብቃትን ማሳደግ፣ የህግ ማዕቀፎችን በመፈተሽ ማረም፣ አሰራር እና አደረጃጀትን ማሻሻል እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ተቋማትን እና ሀገርን ማሻገር እንደሚገባ ለዚሁም የቦርዱ ሰራተኞች የተጀመረውን የሪፎርም ስራ በንቃት እና በብቃት መተግበር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይም በሪፎርሙ ዓምዶች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ለተነሱ ሃሳቦች እና ጥያቄዎችም በተለይ ብቃት ለድርድር የማይቀርብ የሪፎርሙ መሰረት መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበው ቀጣይ ተቋማዊ ዕቅዱ በሪፎርሙ ዓምዶች መቃኘት እንዳለበት አክለዋል፡፡