The Latest from AABE

የግል ኢንሹራንስ ተቋማት አዲሱን የኢንሹራንስ ዓለምአቀፍ የሒሣብ አያያዝ ደረጃ (IFRS 17) መተግበር እንዳለባቸውተገለፀ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም የቢዝነስ ተቋማት ዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝ ደረጃዎችን መተግበር እንዳለባቸው የወጣው አስገዳጅ አዋጅ ቁጥር 847/2006 ተግባራዊ ከሆነ ዓመታት ያለፉት ቢሆንም የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በኢትዮጵያ ካሉ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ 17ቱ IFRS-17 የተሰኘው ዓለም አቀፍ የመድን ድርጅቶች የሂሳብ አያያዝ ደረጃዎች አካል የሆነው ስታንዳርድ በወቅቱ እንዳልተገበሩ አረጋግጧል፡፡

ይህ ስታንዳርድ/ደረጃ IFRS-17 የኢንሹራንስ ኮንትራቶች እንዴት መመዝገብ እንዳለባቸው የሚገልጽ ዓለም አቀፍ የፋይናንሺያል ሪፖርት አቀራረብ ደረጃ ሲሆን በአለምአቀፍ የሂሳብ አያያዝ ደረጃዎች ቦርድ እ.አ.አ. ከጃኑዋሪ 1 ቀን 2023 ጀምሮ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተግባራዊ መሆን የሚገባው ደረጃ ነው፡፡

የቦርዱ የዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ሺፈራው ለሪፖርተር እንዳሉት በሀገራችን የሂሳብ መዝጊያ መሰረት የኢንሹራንስ ተቋማቱ እ.አ.አ. ከሐምሌ 2023 ጀምሮ አዲሱን የኢንሹራንስ ዓለም አቀፍ የሒሣብ አያያዝ ደረጃ (IFRS 17) መተግበር የነበረባቸው ቢሆንም እንዳልተገበሩ ከታወቀ በኋላ በተደረገው ፍተሻ 17 የግል የኢንሹራንስ ድርጅቶች ድጋሚ ሪፖርታቸውን እስከ ነሐሴ 2017 ዓ.ም ድረስ እንዲሰሩ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ዓመታዊ የሂሳብ መግለጫውን በሚገባው ስታንዳርድ መሰረት አዘጋጅቶ እና ኦዲት አስደርጎ ወደ ቦርዱ የማያቀርብ ማንኛውም ሪፖርት አቅራቢ አካል ከቀላል አስተዳደራዊ የገንዘብ ቅጣት እስከ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያደርስ ህግ የማስከበር ሥራ የሚሰራ መሆኑን በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ አዋጅ ቁጥር 847/2006 ላይ ተደንግጓል፡፡

በኢትዮጵያ ካሉ የኢንሹራንስ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮ-ላይፍ ኤንድ ጀነራል ኢንሹራንስ አክስዮን ማህበር በበኩሉ IFRS 17 የተሰኘው የኢንሹራንስ ዓለም አቀፍ የሒሣብ አያያዝ ደረጃ  ዘግይቶም ቢሆን መተግበር መጀመሩን አስታውቋል፡፡ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽመልስ ገብረጊዮርጊስ ለሪፖርተር እንዳሉት “እውነት ነው IFRS 17ን መተግበር የነበረብን ዓመት አልፏል፣ ነገር ግን ደረጃዉን መተግበር ያልቻልነው ቴክኖሎጂው እና የሰው ሀይሉ በሀገር ውስጥ ስላልነበረ ነው፡፡

ኬንያ ብንሄድ የIFRS ባለሙያ እንደልብ ይገኛል፤ ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ከውጭ ሀገር ለማምጣት ደግሞ በትንሹ አንድ ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረግ አለብን፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ከቦርዱ ጋር ተወያይተናል፡፡ እነሱም ችግሩን ለመረዳት ሞክረዋል፡፡ አሁን ላይ ግን ደረጃዉን ለመተግበር እየሰራን ነው፣ እንደተባለው እስከ ነሀሴ ወር 2017 ዓ.ም. ድረስ ሪፖርቱን ሰርተን ለቦርዱ እናቀርባለን“ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የሒሳብ መግለጫ ሪፖርት በተቀመጠው ዓለም አቀፍ የሒሣብ አያያዝ ደረጃ መስፈርት መሰረት መሰራቱንና አለመሰራቱን፣ ሪፖርቶች በIFRS 17 መሰራት አለመሰራታቸውን፣ ሪፖርቶቹን ውድቅ የማድረግና አለማድረግ ሥልጣን የብሔራዊ ባንክ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ (አቤ) መሆኑን አስታውቋል፡፡  

በዘጠኝ ወራት ውስጥ  56 የፋይናንስ ሪፖርቶች በደረጃዎቹ መሰረት መሠራታቸውን የማረጋገጥ ሥራ የተሰራ ሲሆን ስምንት ሪፖርት አቅራቢ አካላት ላይየኋላ ማስተካከያ (IAS 8-retrospective adjustment) እንዲያደርጉ የመጨረሻ ውሳኔ ተሠጥቷል፡፡

የኦዲት ድርጅቶች ዓለም አቀፍ የኦዲት ደረጃዎችን (ISA)፣ የሙያ ስነ-ምግባር (Code of Ethics)፣ እና የኦዲት ጥራት ማረጋገጥ (ISQM1 & ISQM2) ደረጃዎችን ጠብቀው መስራት ይኖርባቸዋል። ይህን ለማረጋገጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሃያ ስምንት የኦዲት ድርጅቶች (በአጠቃላይ ሀምሳ ስድስት የኦዲት ፋይሎች) ላይ የኦዲት የጥራት ምርመራ (audit quality assurance) ሥራ ተከናውኗል፡፡ በተጨማሪም የ17 ኢንሹራንስ ድርጅቶችን የኦዲት ስራ በሰሩ ስድስት የኦዲት ድርጅቶች ላይ የጥራት ማረጋገጥ ሥራ ተሰርቶ ጉዳያቸው ለክስ ሰሚ ተላልፏል፡፡

በተጨማሪም በ56 የሂሳብ ድርጅቶች ላይ ክትትል መደረጉን የገለጹት አቶ አበበ ፍቃድ በወሰዱበት አድራሻ አለመገኘት፣ ባለሙያዎች ደንበኛው ጋር ምንም አይነት ህጋዊ ውል ሳይኖር መስራት እና በሌላ ኦዲተር ስም የኦዲት ሪፖርት ማዘጋጀት፤ ከቦርዱ የወሰደውን የሂሳብ ሙያ ፈቃድ ሳይመልስ ተቀጥሮ መስራት፤ የአደረጃጀት ለውጥ አድርገው በወቅቱ አለማሳወቅ፤ ደረጃውን ጠብቆ ሪፖርት አለማዘጋጀት እና ሌሎች 19(አስራ ዘጠኝ) መዝገቦች የአድራሻ ለውጥ አድርገው በወቅቱ አለማሳወቅ ከተገኙ ክፍተቶች እና እርምጃ ከተወሰደባቸው ግድፈቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡