The Latest from AABE

በIFRS S1 & S2 እና IFRS 18 ላይየግንዛቤማስጨበጫውይይትተካሄደ።

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡ – መስከረም 30/2017 ዓ.ም.   የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በIFRS S1 & S2 እና IFRS 18 ላይ ለዋነኛ ባለድርሻ አካላት በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደ።

መድረኩን የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር የከፈቱት ሲሆን ከፍተኛ የህዝብ ጥቅም ያለባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሪፖርት አቅራቢ አካላት በየጊዜው የሚወጡ እና የሚሻሻሉ አለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎችን ለባለድርሻ አካላት ማስተዋወቅ፣ ማወያየት እና ተግባራዊነቱን መከታተል የቦርዱ ሚና መሆኑን ጠቅሰው IFRS S1 ፣ S2 እና IFRS 18ም የዚሁ አካል መሆኑን አስረድተዋል።

በዕለቱም የቦርዱ የቴክኒክ አማካሪ የሆኑት አቶ ደረጀ ገላና ከዘላቂነት ጋር የተያያዙ ስጋቶችና እድሎች መግለጫ ስታንዳርዱን (IFRS S1 & S2, Risk and opportunity related Sustainability disclosure standards) ምንነት ጽንሰ-ሃሳብ፣ የየሀገራት ተሞክሮ እና የትግበራ የጊዜ ሰሌዳ ያካተተ የመወያያ ፅሑፍ አቅርበዋል። የመወያያ ፅሑፉ የተለያዩ ትኩረት የሚሹ እና አካባቢያዊ፣ ማህበራዊ እና አስተዳደራዊ (ESG) ጉዳዮችን የዳሰሰ ሲሆን ድርጅቶች ስለ ዘላቂነት አፈፃፀም እና ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተፅዕኖዎችን በሂሳብ መግለጫዎቻቸው በማካተት ለተጠቃሚው ባለሃብት ግልጽ እና ወጥ የሆነ መረጃ የማቅረብ ማዕቀፍ መከተል እንደሚገባ ለማሳወቅ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዕለቱም ተጠሪነታቸው ለፌዴራል የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከሆኑ ድርጅቶች የተወጣጡ 100 የልማት ድርጅቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በውይይቱ ላይ በመገኘት የቀረበውን የመወያያ ሃሳብ ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ጠቃሚ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ከዓለም አቀፍ የሂሳብ ሪፖርት መስፈርቶች ጋር የማጣጣም፣ አሰራሩ የህግ ማዕቀፍ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ቀድመው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት ለሌሎች ተምሳሌት መሆን እንደሚያስፈልግ እና ዘላቂነትን መተግበር በዓለም ገበያ ውስጥ ለመተወን ዝቅተኛው መለኪያ እንደሆነም ተወያይተዋል፡፡

በተመሳሳይም የቦርዱ የፋይናንስ እና ኦዲት ማረጋገጥ ደረጃዎች እና ኮርፖሬት ገቨርነንስ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወርቁ ዓለሙ በIFRS 18 ዓላማዎች እና መስፈርቶች ላይ አጠቃላይ መረጃ የሰጡ ሲሆን በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች ውስጥ IFRS 18 በመንግሥት ይዞታ ስር ባሉ ድርጅቶች ውስጥ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ለማሻሻል ያለውን ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡