The Latest from AABE

በኢትዮጵያ የሒሳብ/ኦዲት ሙያ አፈፃፀም የነበረበት እና ያለበት ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ሲካሄድ የነበረ ዳሰሳዊ ጥናት  ሥራ ተከናወነ፡፡

መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም. አዲስ አበባ፡ – ከመስከረም 06 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ የሂሳብ ሙያ (Accoutancy profession) አፈፃፀም አጠቃላይ ሁኔታዎች ላይ ሲካሄድ የነበረ ዳሰሳዊ ጥናት ተጠናቀቀ፡፡

ጥናቱ የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ሶስት ተወካዮችን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች እና ሁለቱም ከተማ መስተዳድሮች የዋና ኦዲተር አመራሮች ውክልና መሰረት የአዲስ አበባ፣የኦሮሚያ፣ የሲዳማ፣ የአማራ እና የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶችን ባካተተ ስምንት ባለሙያዎች ሲከናወን ቆይቶ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ተጠናÌል፡፡

ጥናቱ በዋነኝነት በኢትዮጵያ የሂሳብ/ኦዲት ሙያ አፈፃፀም ወጥነት የሌለው፣ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ከመሰረቱ አባል ሀገራት፣ የኢጋድ፣ የኮሜሳ እና የብሪክስ አባል ሀገር ስትሆን በቅርቡ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አባል እና የዓለም ንግድ ድርጅት አባልም ለመሆን በመስራት ላይ መገኘትን ተከትሎ በነዚህ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ትስስር እና የንግድ ስርዓት ውስጥ ጉልህ ተወዳዳሪ እና ውጤታማ በመሆን ሂደት፤ የዘርፉን ሚና በተገቢው ለመወጣት እንደሀገር ሙያው ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ መፈተሽ፣ በዘርፉ እየሰሩ ያሉ አካላት (የቦርዱን እና የሁሉም ዋና ኦዲተሮችን) የህግ ማዕቀፎች መፈተሽን፣ የመሰል ሀገራት ተሞክሮ መዳሰስ እና ልምድ መቅሰምን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መፍትሔ የሚያገኙበትን እና ከፍተኛ ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ሥርዓቶችን በመላው ሀገሪቱ በውጤታማነት ማሳካት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በጥናቱ ግኝቶች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ የመከሩት የቦርዱ አመራር እና የአምስቱም ክልል ዋና ኦዲተሮች እና የጥናቱ ቡድን አባላት መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ባደረጉት ውይይት ሙያው የህዝብን እና የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ በሚችልበት መልኩ ወጥነት ባለው እና ዓለምዓቀፍ የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሊመራ እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለተግባራዊነቱ ከልባቸው መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የዘርፉን ችግር ከመሰረቱ ለመቅረፍ በተለይ የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎች ኢንስቲትዩት ምሥረታ ትኩረትን የሚሻ መሆኑ በጥናቱ የተጠቆመ ሲሆን ቦርዱም የክትትል፣ ቁጥጥር እና የድጋፍ ሥራውን ማጠናከር እንዳለበት ተገልጿል፡፡