The Latest from AABE

የአፍሪካ አካውንታንቶች ፌዴሬሽን አውደ-ጥናት ተካሄደ

የአፍሪካ አካውንታንቶች ፌዴሬሽን /Pan African Federation of Accountants, PAFA/ ከመጋቢት 10/2016ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀናት የቆየ አውደ-ጥናት በአዲስ አበባ ራዲሰን ብሉ ሆቴል ከ22 የአፍሪካ አባል አገራት የመጡ 38 የሒሳብ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሄደ፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚነስቴር ዴኤታ እና የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ የሂሳብ እና የኦዲት ሥራ ላይ የጥራት ችግርን በመቅረፍ ጥራት ያለው፣ ተዓማኒ እና በመላው ዓለም ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችል የኦዲት ሪፖርት ማዘጋጀት እንዲቻል ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የዘርፉ ባላሙያዎች በመምከር በአህጉር ደረጃ የሚናበብ፣ ድንበር የማይገድበው በሁሉም አገራት የሚተገበር የአሰራር ማንዋል በማጽደቅ በዘርፉ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር የሚፈታ ውይይት ሊያካሂዱ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ አካውንተንሲ ፌዴሬሽን /PAFA/ መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገ ሲሆን የመድረኩ ዓላማም በአህጉር ደረጃ ወጥ የሆነ የኦዲት ሪፖርት እንዲኖር የአሰራር ስርዓት ዘርግቶ ጥራት ያለው፣ ተዓማኒ እና በመላው ዓለም ተቀባይነት ያለው የኦዲት ሪፖርት እና ባለሙያ ማፍራት የሚያስችል ሁሉም አፍሪካዊያን የሚጠቀሙበት የአሰራር ማንዋል ለማጽደቅ መሆኑን የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተርዋ በንግግራቸው የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድም በፌዴሬሽኑ አባል ከሆነ አራት ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ቀደም ብለው የሂሳብ እና የኦዲት ሙያን መከታተል እና መቆጣጠር ከጀመሩ ቀደምት የፌዴሬሽኑ አባል አገራት ልምድ እና ተሞክሮ እየወሰደ በሪፖርት አቅራቢ ተቋማት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አተገባበር ደረጃዎችን በማስተግበር የሕዝብ ጥቅምን ለማስጠበቅ ክትትል እና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡