ጥር 22/2018 ዓ.ም. አዲስ አበባ፣ የኢትዮጰያ የሒሣብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ የሙያ እና ሙያ ማህበራት ክትትል እና ቁጥጥር ሥራ አስፈፃሚ ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም. ለኦሮሚያ ክልል የሒሣብ እና ኦዲት ባለሙያዎች እና ጥር 20-21/2018 ዓ.ም. ለትግራይ ክልል የሒሣብ እና ኦዲት ባለሙያዎች በተሻሻለው የሙያ እና ሙያ ማህበራት ፍቃድ እና ዕውቅና መመሪያ ቁጥር 1096/2017 አተገባበር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጠ፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫው በዋነኝነት በሒሣብ እና ኦዲት ሙያ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የ2018/19 የሙያ ፍቃዳቸውን ሲያድሱ እንግልት እንዳይገጥማቸው ቅድሚያ መመሪያውን መረዳት እንደሚገባ የዋና ዳይሬክተር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ሺፈራው የገለፁ ሲሆን መመሪያው በረቂቅ ደረጃ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የተካሄደበት ቢሆንም በተለይ በትግበራ ወቅት ባለሙያው ትኩረት ሊሰጣቸው በሚገቡ እና በአጠቃላይ አሰራር ላይ ግልፅ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ መወያየት ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ከ2014 ዓ.ም. በፊት ከክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቶች የሙያ ፍቃድ አውጥተው በሙያው እያገለገሉ ያሉ እና በቀጣይ በቦርዱ በኩል የሙያ ፍቃዳቸው እንዲታደስላቸው የሚፈልጉ ባለሙያዎች አገልግሎቱ እንዲሰጣቸው የቦርዱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ባስተላለፈው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ እንደሚደረግም ተብራርቷል፡፡
በዚሁ መሰረት የሙያ እና ሙያ ማህበራት ክትትል እና ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈፃሚው አቶ ደገፋ በንቲ በመመሪያው ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተሻሻለው የሙያ ፍቃድ እድሳት የሚከናወንበት Eservices አጠቃቀም ላይም ገለፃ አድርገዋል፡፡
ቦርዱ ቀድሞ ከነበሩት የሂሳብ ሙያ እና የኦዲት ሙያ አገልግሎቶች በተጨማሪ የፐብሊክ ኦዲተር ሙያ እንዲሁም የጣምራ አገልግሎቶች የተጨመሩ መሆኑን ገልፀው አመልካቾች በኦንላይን ለአዲስ ፍቃድም ይሁን ለእድሳት ሲያመለክቱ ድግግሞሽ እንዳይኖር ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና ለዚህም የተዘጋጀውን በድምፅ እና በምስል የተደገፈ አጋዥ ቪዲዮ መጠቀም ችግሩን እንደሚያቀልላቸው አስረድተዋል፡፡
በውይይቶቹም ከክልሎች ጋር እየተከናወነ የነበረው የቅንጅት ስራ ፍላጎትን ማጠናከር፣ የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሣብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ሥራ ለመጀመር ያለበትን ሁኔታ ማፋጠን እና የሙያውን ጥራት ለማሳደግ የክትትል፣ የድጋፍ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው በተለይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር የተሰራው የቅንጅት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላትም ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ መከናወን እንዳለበት አፅንዖት ተሰጥቷል፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫው በተለያዩ ጊዜያት ለሐረሪ፣ ለሲዳማ፣ ለአማራ፣ለሰመራ እና ለድሬደዋ የሒሳብ እና ኦዲት ባለሙያዎች የተሰጠ መሆኑ ይታወሳል፡፡