The Latest from AABE

“ባለሙያው ከሙያዊ ስነ-ምግባር ውጪ የሆኑ ተግባራትን ሊፀየፍ ይገባል!!” የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር

ቦርዱ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ከተፈቀደላቸው የሂሳብ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ጋር የጋራ የግንዛቤ መፍጠሪያና የውይይት መድረክ አካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 04 እና 05 ቀን 2018 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የሒሣብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከ500 በላይ ለሚሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የተፈቀደላቸው የሒሣብ ባለሙያዎች/ድርጅቶች በሙያዊ ስነ -ምግባር ላይ እና የሒሣብና ኦዲት ባለሙያዎች ፍቃድ አሰጣጥ እና የሂሳብ ሙያ ማህበራት ምዝገባ መመሪያ ቁጥር 1096/2017 ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫና የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

በአገራችን የኢኮኖሚ ሪፎርም እየተተገበረ እንደመሆኑ፤ የአካውንተንሲ ሙያ ሚናው ልቆ መውጣት እንዲችል በተቀመጠ የአሰራር ስርዓት መሰረት ሙያዊ ስነ-ምግባርን ተላብሶ ሃላፊነትን መወጣት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሒሣብ ደረጃዎችን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ የግንዛቤ መፍጠሪያና የመወያያ መድረክ መሆኑን የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር በመድረኩ መክፈቻ ላይ ገልጸዋል፡፡በመድረኩም በቦርዱ የፋይናንስ፣ ኦዲትና ማረጋገጥ ደረጃዎች እና ኮርፖሬት ገቨርናንስ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ወርቁ ዓለሙ የሙያ ስነ-ምግባርን በተመለከተ ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን፣ የህግ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ነጋሽ የየሂሳብና የኦዲት ባለሙያዎች ፍቃድ አሰጣጥና የሂሳብ ሙያ ማህበራት ምዝገባ መመሪያ ቁጥር 1096/2017 ላይ ገለጻ አቅርበዋል፡፡

በገለጻውም በዋናነት በዘርፉ ያሉ የሒሣብ ባለሙያዎች ስራቸውን ሲተገብሩ ሊላበሱ የሚገባቸው ሙያዊ ስነ-ምግባር ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ እንዲሁም የ1096/2017 ማሻሻያ አስፈላጊነት፣መመሪያው ያካተታቸው አዳዲስ ጉዳዮች ሠፊ ትንታኔ ቀርቦባቸዋል፡፡የቀረቡትን ገለጻዎች መነሻ በማድረግ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር የሙያው ባለቤት እኛው እንደመሆናችን ከሙያተኛው አንጻር በማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ግንዛቤ ለመለወጥ ራስን በአግባቡ መፈተሽና የምንሰራቸውን ስራዎች እንደየሃላፊነታችን አዋጅን፣ደንብን፣ስታንዳርዶችን፣የሙያ ስነ-ምግባርን ያከበሩ እንዲሆኑ መስራት እና ቦርዱ ለሚያደርገው የክትትልና ድጋፍ ስራ ምቹ ሆኖ መገኘት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

አክለውም ቦርዱም በቀጣይ ድጋፍ ያላደረገበት አግባብ ካለ መርምሮ ወደፊት የሚሄድበትን ሁኔታ ያመቻቻል ብለዋል፡፡

መድረኩ በክልሎች ካሉ የተፈቀደላቸው የሒሣብ አዋቂዎች ጋርም በቅርቡ በተመሳሳይ መልኩ የሚከናወን ይሆናል፡፡