መስከረም 15/2018 ዓ.ም. አዲስ አበባ፣
የኢትዮጵያ የሒሣብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 847/2006 የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብን ኢትዮጵያ ተቀብላ ተግባራዊ ለማድረግ የተደነገገውን የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎችን ለማስተግበር በደንብ ቁጥር 332/2007 የተቋቋመ ተጠሪነቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር የሆነ ተቆጣጣሪ የመንግስት ተቋም ነው፡፡
የቦርዱ መቋቋም ዋና አላማ በሪፖርት አቅራቢ አካላት (በንግዱ ማህበረሰብ) የሚቀርቡ የፋይናንስ እና ተያያዥነት ያላቸውን ሪፖርቶች አዘገጃጀት እና አቀራረብ ጥራት ማስጠበቅ፣ የኦዲተሮች እና የሒሣብ ባለሙያዎችን የሙያ ደረጃ ማስጠበቅ፣ የሒሣብ አያያዝ እና የኦዲት አገልግሎትን ጥራት ማስጠበቅ፣ የሒሣብ ሙያ የሕዝብ ጥቅምን ማስጠበቁን ማረጋገጥ እና የሒሣብ እና የኦዲት ባለሙያዎችን የሙያ ነፃነት ማስከበር ነው፡፡
በሪፖርት አቅራቢ አካላት የሚቀርቡ የፋይናንስ እና ተያያዥነት ያላቸውን ሪፖርቶች በአዋጁ አንቀፅ 5 (1) መሠረት አለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች (IFRS) ፣ የመካከለኛ እና አነስተኛ ድርጅቶች አለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች (IFRS for SMEs) ፣ እና ለበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የሚያገለግል አለምአቀፍ የፐብሊክ ሴክተር የሒሣብ አያያዝ ደረጃዎች(IPSAS)ን ተፈፃሚ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም በአንቀፅ 12 ንዑስ አንቀፅ 3 ማንኛውም የተመሰከረለት የኦዲት ባለሙያ የሙያ ሥራውን ሲያከናውን ቦርዱ ለተመሰከረላቸው ኦዲተሮች ባወጣቸው የተለዩ የኦዲት ደረጃዎች(ISA) ያስቀመጣቸውን አነስተኛ መስፈርቶች ማክበር እንዳለበት ይደነግጋል፡፡
የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የተቋቋመው ይህን ዓላማ ለማሳካት ነው፡፡ ይህ ስታንዳርድ ሲተገበር በፋይናንሻል ስቴትመንት አቅራቢዎች እና ተጠቃሚዎች፣ በግብር ከፋዩ እና በግብር ሰብሳቢ ተቋማት፣ በኢንቨስተሩ ወይም በባለሀብቶች ወይም በውሳኔ ሰጪዎች እና በአቅራቢዎች መካከል መተማመን ለመፍጠር ነው፡፡ የቢዝነስ ተቋማት የሒሣብ መግለጫዎቻቸውን ሲያዘጋጁ በምን አሰራር (ስታንዳርድ) እንደሚያዘጋጁ መታየት አለበት፡፡
ስለዚህ ይህንን መተማመን ለመገንባት የተቀመጡ ስታንዳርዶች ወደ ተግባር መግባት አለባቸው፡፡ ፋይናንሻል ስቴትመንቶችን/የሒሣብ መግለጫዎችን የሚያዘጋጁ፣ የተዘጋጁትንም መግለጫዎች ጥራት የሚያረጋግጡ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ለነዚህ ባለሙያዎች የሙያ ፍቃድ የመስጠት፣ ፍቃዳቸውን የማደስ፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን መሥራት ማለትም ባለሙያዎች አለም አቀፍ ስታንዳርዶችን አውቀው ከሌሎች ሀገራት ባለሙያዎች ጋር እኩል ተወዳዳሪ ሆነው፣ የሀገር ውስጥን ፍላጎት አሟልተው እና ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለዓለም ገበያ በተለያየ መልኩ እየከፈተች ባለችበት በአሁኑ ሁኔታ ብቁ እንዲሆኑ ማገዝ፣ ህግ ጥሰው ሲገኙም ተጠያቂ የሚሆኑበትን ህጋዊ አሰራር ተከትሎ ህግን በማስከበር ሙያው ብሔራዊ ክብርን እና የህዝብን ጥቅም ማስጠበቁን ማረጋገጥ የቦርዱ ተግባራት ናቸው፡፡
እነኚህን ተግባራት እውን ለማድረግ ቦርዱ ከሚመለከታቸው መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ከሀገር ውስጥ እና ሌሎችም ተባባሪ እና አጋር ባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራል፡፡
ቦርዱ ባለድርሻ ብሎ ከለያቸው አካላት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አንዱ ሲሆን ወደ ቢሮው የሚቀርቡ የሂሳብ መግለጫዎች በአዋጅ ቁጥር 847/2006 በተደነገገው መሰረት ዓለም ዓቀፍ ደረጃዎችን በጠበቀ መልኩ ተዘጋጅተው እና ኦዲት ተደርገው መቅረብ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ በቅንጅት መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከቢሮው ጋር አብሮ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2016 ዓ.ም. ቢሮው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአስራ አንዱም ክፍል ከተሞች 36,729 የሂሳብ መዝገቦችን በጥናት በመመርመር የተጭበረበሩ መሆናቸውን እና በዚህም 10.65 ቢሊዮን ብር ለመንግስት ገቢ መሆን የነበረበት ሀብት ሊሰወር እንደነበረ እና ይህን ገቢ እንዲሰወር ያደረጉት 9,587 የሚሆኑ ባለሙያዎች መሆናቸውን ለቦርዱ ካቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡
ሆኖም በበጀት ዓመቱ በቦርዱ የሙያ ፍቃድ ተሰጥቷቸው በሂሳብ እና ኦዲት ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ቁጥር ከ1,500 የማይበልጡ እና ቀሪዎቹ 8,000 ያክል የሚሆኑቱ በህገ ወጥ የሚሰሩ ወይም ከሌላ አካል ፍቃድ የተሰጣቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ እና ቢሮው የጠቀሰው ቁጥር የተሳሳተ መሆኑን በማስረዳት በቦርዱ ፈቃድ የተሰጣቸውን ባለሙያዎች ዝርዝር ቢሮው እንዲያውቀው ተደርጓል፡፡ ቢሮው ከተላከለት ዝርዝር ውስጥ በቅድመ-ምርመራ ስራው 823 ባለሙያዎችን ነጥሎ በማውጣት ለወንጀሉ ተባባሪ በመሆናቸው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለቦርዱ ጥያቄ ማቅረቡም ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ቦርዱ በግብር ስወራ የተባበረን ባለሙያ ከማንኛውም አካል ጥቆማም ሆነ አቤቱታ ሲቀርብለት የተሟላ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ህግ የማስከበር እና የህዝብን ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ለማስረዳት የተሞከረ ሲሆን ቢሮው እንዲታገዱ፣ ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ እና መሸለም ያለባቸውም አካላት ካሉ የጠየቃቸውን ባለሙያዎች ዝርዝር የተሟላ መረጃ እንዲያቀርብ ቢጠየቅም ምንም አይነት ምላሽ አልተሰጠም፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ሃሳብ መፍትሄ ሳያገኝ በቁጥር 10/1/4222/18 በቀን 12/01/18 ዓ.ም. በተፃፈ ደብዳቤ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የግብር ከፋዮችን ሒሣብ መዝገብ አዘጋጅተው ካቀረቡ ባለሙያዎች መካከል በተሠራው የቅድመ-ኦዲት ሥራ የጎላ ጥፋት የፈፀሙ አስር (10) ባለሙያዎች ሀገር ማግኘት የሚገባትን ጥቅም የሚያሳጣ ሥራ ሰርተዋል እና እርምጃ ተወስዶ በአምስት ቀናት ውስጥ እንድናሳውቅ በደብዳቤ ቢጠየቅም፣ ቦርዱ አጣርቶ ሳያረጋግጥ ደብዳቤው ወደቦርዱ በተላከበት ዕለት ቢሮው በመገናኛ ብዙሀን በኩል መረጃውን እንዲወጣ ማድረግ እንደ ባለድርሻ አካል የቅንጅት ሥራው ላይ እንቅፋት የፈጠረ ሆኗል፡፡
በሌላ በኩል ግብር መሰወር የወንጀል ኃላፊነት የሚያስከትል በመሆኑ የታክስ ወንጀል ጉዳዮች የሚታዩበት ሥነ-ሥርዓት እና ለቦርዱ በተሰጠው ህጋዊ ሥልጣን መሰረት ሥራውን ሊያሰራ የሚያስችል የቅድመ-ኦዲት ምርመራ ሳይሆን የተሟላ የኦዲት ምርመራ ሪፖርት በመሆኑ የአንድን ባለሙያ ፍቃድ ለመሰረዝም ሆነ ለማገድ አዳጋች የሚያደርገው ስለሆነ ጊዜ ወስዶ መመርመርና ማየትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡