The Latest from AABE

ቦርዱ ከሁሉም የሀገራችን የሂሳብና ኦዲት ሙያ ማህበራት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በኢትዮጵያ የተመሠከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት (ETiCPA) ምስረታ መሠረታዊ ጉዳዩች ላይ ተወያየ፡፡

“በተለመደው መንገድ ሄደን በሙያው ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ለውጥና የህዝብን ጥቅም የሚያስጠብቅ ውጤት ማምጣት አንችልም።”

አቶ ፍቃዱ አጎናፍር፣ የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር እና የኢንስቲትዩቱ ጊዜያዊ አስተዳደር ም/ቤት ሰብሳቢ

መስከረም 10/2018ዓ.ም. አዲስ አበባ፣የኢትዮጵያ የሒሣብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ከአዲስ አበባ እና ከክልሎች የሂሳብና ኦዲት ሙያ ማህበራት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በኢትዮጵያ የተመሠከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት(ETiCPA) ምስረታ መሠረታዊ ጉዳዩች ላይ ተወያይቷል።

የውይይቱ ዋነኛ ዓላማ እንደአገር በቂ እና ብቁ የተመሠከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎችን ማፍራት የሚችል ኢንስቲትዪት ለመገንባት እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ በሙያው ያሉ ማህበራት አመራሮች እና አባሎቻቸው ያለውን ሂደት ተገንዝበው ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ላይ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል ።

ቦርዱ እንደአገር መሆን በሚገባው ቁመና ልክ ሆኖ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እየፈጠረ ያለውን ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለማቀፋዊ ጫና መቋቋም የሚያስችል፣ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብር እና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የሪፎርም ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር እና የኢንስቲትዩቱ ጊዜያዊ አስተዳደር ም/ቤት ሰብሳቢ አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ገልጸዋል።

አክለውም በተለመደው መንገድ ሄደን የተሻለ ለውጥና ውጤት ማምጣት አንችልም። ከተለመደው ወጣ ብሎ ማሰብና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለ ስራን በመስራት ሙያውንም ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በመድረኩም የኢንስቲትዩቱን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1372/2017 የቦርዱ የህግ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን ነጋሽ በስፋት ያቀረቡ ሲሆን የኢንስቲትዩቱ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ደረጄ ገላና ኢንስቲቲዩቱ ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ እና ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት እየተከናወኑ ያሉ አንኳር ተግባራት ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል።

በቀረቡት ገለጻዎች መነሻነትም ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። ኢንስቲትዩቱን ወደ ስራ በማስገባት ሀገራችን እንደታሪኳ ጠንካራ ባለሙያ በማፍራት በተለይ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለዓለም ገበያ ክፍት ባደረገችበት ወቅት ቦርዱ እና ኢንስቲትዩቱ ህዝብን እና ሀገርን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት የሙያ ማህበራቱ አመራሮች እና አባሎቻቸው በጋራ በመሆን የሚጠበቅባቸዉን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።