The Latest from AABE

የኦዲት ባለሙያዎች/ድርጅቶች የኦዲት ጥራትን ለማሻሻል ከቦርዱ ጋር ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

ሰኔ16/2017 ዓ.ም. አዲስ አበባ፣ የፋይናንሺያል ሪፖርትና ኦዲት ጥራት ግምገማ አፈጻጸምን ለማሻሻልና ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ የውይይት መድረክ ከኦዲት ባለሙያዎች ጋር ተካሂደ፡፡

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት እያስመዘገበች ባለው ዕድገት ላይ የኦዲት ባለሙያዎች/ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ከመሆኑም ባሻገር ሀገር ከዚህ ሙያ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማስጠበቅ የሚገባ በመሆኑ፤ ሙያውን ለማሳደግና ደረጃውን የጠበቀ የኦዲት ጥራት ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ተግባራዊ በማያደርጉት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል መግባባትን ለመፍጠር በጋራ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር በመድረኩ መክፈቻ ላይ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩም ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተካሄደው የኦዲት ጥራት ግምገማ የታዩ ተግዳሮቶች እና መልካም አጋጣሚዎች የተዳሰሱ ሲሆን በተለይ በሪፖርት አቅራቢ አካላት መካከል ያሉ የአስተዳደር ተግዳሮቶች፣ የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት እና የእውቀት ክፍተቶች፣ ከውጤቶቹ ወይም ከሴክተሩ ከሚጠበቁት ጋር ሲነጻጸር ያልተመጣጠነ ጥረት፣ አለማቀፍ ደረጃዎች በቂ ግንዛቤ አለማግኘቱ፣ ውጤታማ ያልሆነ የኮሙኒኬሽን ባህል፣ ከመስፈርት ጋር ያልተጣጣመና በቂ ያልሆነ የኦዲት ሰነድ፣ ከኦዲት ጥራት ጋር የተያያዙ ዋነኞቹ ተግዳሮቶች መሆናቸው በቦርዱ የቴክኒካል አማካሪ አቶ በርናባስ ጌቱ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ማደግና የገበያ መስፋፋት፣ የህግ ማሻሻያዎች እና የተሻሻሉ ስታንዳርዶች፣ ቦርዱ በሪፎርም ሂደት ውስጥ መሆኑ፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እና የባለሙያዎች ልማት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ የኮርፖሬት አስተዳደር ግንዛቤን ማደግ፣ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ መመስረት የኦዲት ጥራትን ለማሻሻል በጥናቱ እንደ መልካም አጋጣሚ የተለዩ መሆናቸው ተነስቷል፡፡ እንዲሁም ሌላው የቦርዱ ቴክኒካል አማካሪ አቶ ፍቅሩ ፋንታሁን የፋይናንሻል ሪፖርት አዘጋጆች በባለቤትነት እና በጥልቅ ዕውቀት የሒሣብ መግለጫዎቻቸውን በደረጃዎቹ መሠረት አለማዘጋጀት፣ የፋይናንስ ሪፖርትን ከIFRS ጋር የማስተሳሰር ባህል አለመጎልበት፣ የፋይናንስ ቡድን የዕውቀት ማነስ እና ትኩረት ያለመስጠት በፋይናንሺያል ሪፖርት ግምገማ የታዩ ዋና ዋና ግኝቶች መሆናቸውን አቅርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

በመሆኑም የኦዲት ጥራትን እንደአገር በተገቢው ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ የተቀመጡ ስታንዳርዶችን በመፈጸም ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን ባለሙያው ብቃት እና ተወዳዳሪነትን መጎናፀፍ እንዳለበት፣ የማስተማር ወቅት ማብቃት እና ህግ ማስከበር ላይ ማተኮርም እንደሚገባ፣ ባለሙያው ከሀገርም አልፎ ለሌሎች መትረፍ የሚያስችል በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን መከተል እና የአቅም ግንባታ ጉዳዮች ላይ መተኮር እንዳለበት ጭምር ከተወያዮች ተሰንዝራል፡፡ በተያያዘም በሙያው ብቃትን ማሳደግና የፋይናንስ ሪፖርትን ከIFRS እና የኦዲት ደረጃዎች ጋር የማስተሳሰር ባህል እንዲጎለብት ግንዛቤ መፍጠር ተገቢ መሆኑ በምክረ-ሃሳብ ተመላክቷል፡፡

በመጨረሻም ቦርዱ እስካሁን ባለው ሂደት የኦዲት ሪፖርት ጥራትን ለማስጠበቅ ግንዛቤን መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም አብዛኛው ባለሙያ ከተባባሪነት ይልቅ ለሙያው ማንሰራራት ተግዳሮት መሆኑን በመጠቆም በቀጣይ አሁን ያሉት ዓለምአቀፋዊና አገርአቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ስለሚያስገድዱ ወደ ተጨባጭ ዕርምጃና ተጠያቂነትን ወደማስፈን መግባት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ከኦዲት ባለሙያዎች/ድርጅቶች ጋር በመደጋገፍና በመተጋገዝ እንደሚሰራ ተ/ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡