The Latest from AABE

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከዓለም ባንክ ጋር በጋራ በመሆነም በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች የሚያፈራ ኢንስቲትዩት መቋቋሙን መሰረት በማድረግ ከግንቦት 11-13 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የPan African Federation of Accountants(PAFA) እና የናይጄሪያ፣ የየጋንዳ፣ የደቡብ አፍሪካ እና የኬንያ PAOs or public accountancy organizations ተሞክሮአቸውን ያካፈሉበት የምክክር መድረክ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ ሃገራት የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ሀያት ሪጀንሲ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

መድረኩን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ሲሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ጠንካራ የሂሳብ ሙያ ሃገራችን ለተያያዘችው የለውጥ ጉዞ ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑን ጠቁመው በሃገራችን የሚቋቋመው የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ለዘርፉ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

የዓለም ባንክ ዲቭዥን ዳይሬክተር የሆኑት ማርያም ሳሊም በበኩላቸው የምክክር መድረኩ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ መዘጋጀት በራሱ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር እና በጋራ መስራት እንዲቻል ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው ለሙያው መጎልበትም ሰፊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር በበኩላቸው የቦርዱን አመሰራረትና እስካሁን ድረስ በሂሳብ ሙያ ላይ የነበረውን ሚና የሚያመላክት ታሪካዊ ዳራ ባቀረቡበት ወቅት ሙያው በተፈለገው ደረጃ አለማደግና ተወዳዳሪ ባለሙያን ለማፍራት ማነቆ ከሆኑ ጉዳዮች የመጀመሪያው የዘርፉ ባለሙያ ቁጥር ማነስና የእውቀት ውስንነት መኖሩን ጠቁመው እንደሃገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የሂሳብ ባለሙያዎችን የሚያፈራ ኢንስቲትዩት መቋቋሙ ዋና ዓላማ የሂሳብ ሙያን ማሳደግና ቀጣይነቱን ማረጋገጥ፤ የሂሳብ ሙያ የህዝብ ጥቅምን ማስጠበቅና ማረጋገጥ በመሆኑ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት ያግዛል ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተለያዩ ጽሑፎችና የተለያዩ ሃገራት ተሞክሮዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን መድረኩ በነገው ዕለትም ቀጥሎ ይውላል፡፡