በኢትዮጵያ በአካውንተንሲ ሙያ ታሪክ ጉልህ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት (ETICPA) ማቋቋሚያ አዋጅ መጋቢት 04 ቀን 2017 ዓ.ም. በኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1372/2017 ሆኖ ፀድቋል።
የኢንስቲትዩቱ ማቋቋሚያ አዋጅ የፀደቀው ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎችን ቀርፃ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ባለችበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነው። ተቋሙ በግልም ሆነ በመንግስት ተቋማት ውስጥ ግልፅነት እና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ከፍተኛውን የሂሳብ አያያዝ፣ ኦዲት እና የፋይናንሺያል ሪፖርት መረጃዎችን የማስተዋወቅ እና የማሳደግ አላማ አለው።

የኢትየጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ የወደፊት የሂሳብ አያያዝ ሂደት ውስጥ ያለውን ጠቀሜታ በማውሳት፣ “የኢንስቲትዩቱ መቋቋሚያ አዋጅ መፅደቅ ለሙያው ዕድገት አዲስ ከፍታን የሚያመላክት ሲሆን በሂሳብ ባለሙያዎች መካከል ታማኝነትን፣ ሙያዊ ብቃትን እና ጥራትን ለማጎልበት ባለን ቁርጠኝነት ለሀገራችን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለተወዳዳሪነት፣ ለዕውቀት መጋራት፣ እና በመላ ሀገሪቱ ላሉ የሒሳብ ባለሙያዎች አቅም ማጎልበት መድረክ ሆኖ ያገለግላል። የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋም ሙያውን ለማጠናከር እና በመጨረሻም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ትልቅ አቅም ነው።