የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ተነሳሽነት በኢትዮጵያ በሚገኙ የመንግስት ተቋማት ተግባራዊ ለማድረግ ለታሰበው የአለም አቀፍ የመንግስት ዘርፍ የሂሳብ አያያዝ ደረጃዎች (IPSAS) አተገባበር ላይ ህዳር 04 ቀን 2017 ዓ.ም ከቢል ጌትስ ፋውንዴሽን አመራሮች ጋር በቦርዱ የስብሰባ አዳራሽ ተወያየ።
በውይይቱም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፋይናንስ ባለሙያዎች እና የቢል ጌትስ ፋውንዴሽን ተወካዮችን ጨምሮ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።
“የ IPSAS ትግበራ የመንግስት ተቋማትን የፋይናንስ ጤናማነት ከማጠናከር ባለፈ በዜጎች ላይ እምነት ለመፍጠር ያስችላል ብለን እናምናለን” ሲሉ የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ተናግረዋል።
የIPSASን ውጤታማ ትግበራ ለማረጋገጥ በምርጥ ተሞክሮዎች ላይ በመመስረት ቦርዱ በትግበራ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ወቅት የቴክኒክ ድጋፍ ይሰጣል፣ ለመንግስት ዘርፍ የሂሳብ ባለሙያዎች፣ ኦዲተሮች እና የፋይናንስ አስተዳዳሪዎች የስልጠና እና የአቅም ግንባታ ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ሲሆን ይህም ደረጃዎቹን በመተግበር ወቅት አስፈላጊ ክህሎቶችን እና ዕውቀትን ለመገንባት ይረዳል ብለዋል።
የቢል ጌትስ ፋውንዴሽን ተወካዮች እነዚህን ጥረቶች
ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸው ፋውንዴሽኑ የተሻለ የፋይናንስ አስተዳደርን በማስፈን የህዝብ ኑሮን ለማሻሻል እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያለውን ተሞክሮ በኢትዮጵያም ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎች አዋጅ 847/2006 መሰረት የሪፖርት አቅራቢ አካላት ምዝገባ እና መለያ መስፈርቶችን በማውጣት ጉልህ የህዝብ ጥቅም ያለባቸው፣ ሌሎች የህዝብ ጥቅም ያለባቸው እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት የትግበራ ፍኖተ-ካርታ በማውጣት ተግባራዊ በማስድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ይሁንም እንጂ አብዛኞች ሪፖርት አቅራቢ አካላት በህጉ መሰረት ለድርጅታቸው የሚገባውን ደረጃ በወቅቱ በመተግበር እና ኦዲት በማስደረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን በወጣው የትግበራ ፍኖተ-ካርታ መሰረት ድርጅታቸውን በቦርዱ ያላስመዘገቡ እና ተገቢውን ደረጃ ተግብረው እና ኦዲት አስደርገው ወደ ቦርዱ ያላቀረቡ ሪፖርት አቅራቢ አካላት ላይ ህግ የማስከበር ስራ እየተገበረ መሆኑም ይታወቃል፡፡