ጳጉሜን 03 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ፡ – የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ለሰራተኞቹ ይሰጥ የነበረው የስራ ስነ-ምግባር ስልጠና ፕሮግራም በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል። በስራ ቦታ የሚከናወኑ የስራ እና ሰራተኛ ከእርስበርስ እና ደምበኛ ጋር የሚደረግ ግንኙነት ሙያዊ ሥነ-ምግባርን የተላበሰ መሆን እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቶታል።
ሁሉንም የቦርዱ ሰራተኞች የተሳተፉበት ይህ ሥልጠና፣ ሠራተኞች ሥነ ምግባርን የሚፈታተኑ ተግባራትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመወጣት የሚያስችሉ ግንዛቤዎችን ለማስታጠቅ የሚረዱ ውይይቶችንም ያካተተ ነበር።
የቦርዱ ም/ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጽዋዬ ሙሉነህ እንደገለፁት ስልጠናው በአጠቃላይ ለህዝብ አገልግሎት ለሚሰሩና በተለይም በስራ ቦታ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ፣ ተጠያቂነትን ለማዳበር እና ሙያዊ አገልግሎትን ከማጎልበት ረገድ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል።
የሥነ ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የስራ ባልደረባ የሆኑት አቶ አለማየሁ በሰጡት ስልጠና እንደተናገሩት፣ “የሠራተኞች የሥራ ሥነ-ምግባር ሥልጠና ማግኘ ት የግልጽነት ባህልን ለማ ጎልበት፣ የቦርዱን እሴት ለማጠናከር እና ጥሩ የሥራ አካባቢ እንዲኖር በማድረግ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችል ሞራልና ምርታማነትን እንደሚጨምር ገልፀዋል። ስልጠናውም እንደ ታማኝነትነት ፣ ተጠያቂነትና ግልጽ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግን የመሳሰሉ ወሳኝ ርዕሰ ጉዳዮችን ያካተተ ነበር ።
“ቦርዱ የሥነ ምግባር እና የኃላፊነት ባህልን ለማሳደግ ቁርጠኛ ነው” ሲሉ ወ/ሮ ጽዋዬ በመዝጊያ ንግግራቸው ላይ የተናገሩ ሲሆን ስልጠናው የቦርዱ ሰራተኞች ስለ ሥነ-ምግባር ተግባራት ያላቸውን ግንዛቤ ከማሳደግ ባለፈ እሴቶቹንም በመጠበቅ የጋራ ቁርጠኝነታቸውን እንደሚያጠናክር አብራርተዋል።
በወቅቱም የቦርዱ መለያ አዲሱ ብራንድ እና ድረ-ገፅ ለሰራተኞች የማስተዋወቅ እና የአጠቃቀም ማብራሪያ ቀርቧል፡፡