ጳጉሜን 04 ቀን 2016 ዓ.ም፡ – አዲስ አበባ፡ የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ከቦርዱ የሒሳብ ሙያ ፍቃድ ተሰጥቷቸው በሙያው ሲያገለግሉ በነበሩ ስድስት ባለሙያዎች የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ህጎችን በመተላለፋቸው ምክንያት ህጋዊ እርምጃ የወሰደባቸው መሆኑን አሳወቀ፡፡
የቦርዱ የህግ ማስከበር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወርቁ አዲስ እንደተናገሩት ምርመራ ተካሂዶባቸው በቀረበባቸው ክስ የቦርዱ የክስ ሰሚ ችሎት በACF15265 የምዝገባ የምስክር ወረቀት የተመዘገበ ፍቃዱ ማሞ የሒሳብ አዋቂ ድርጅት በሂሳብ እና ኦዲት ባለሙያዎች ፍቃድ አሰጣጥ እና የሂሳብ ሙያ ማህበራት ምዝገባ መመሪያ ቁጥር 805/2013 አንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ በተደነገገው መሰረት ውሳኔው ከተላለፈበት ነሀሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የድርጅት የምዝገባ ምስክር ወረቀቱ የተሰረዘ መሆኑን የገለፁ ሲሆን የምስክር ወረቀቱን ወደ ቦርዱ መመለስ እንዳለባቸው እና ከቦርዱ ድረ-ገፅ የሂሳብ እና ኦዲት ባለሙያዎች እና ድርጅቶች ዝርዝርም የሚወገድ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
በተመሳሳይም አራት ባለሙያዎች በገንዘብ ቅጣት እና አንድ ባለሙያ የማስጠንቀቂያ ቅጣት የተላለፈባቸው መሆኑን አቶ ወርቁ አብራርተዋል፡፡
ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት በሚደርሱት የህዝብ ጥቆማ እና በሚያከናውናቸው የክትትል እና ቁጥጥር ተግባራት በሚያገኛቸው የሕግ ጥሰቶች እንደየ የሕግ ጥሰቶቹ መጠን አስተማሪ ምክሮች እና ማስጠንቀቂያዎችን የሚሰጥ ቢሆንም በህዝብ ላይ ጉልህ ጥፋት የሚያደርሱ ተግባራትን የማይታገስ እና ወደ ህግ በማቅረብ ህግን የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሙያ እና ሙያ ማህበራት ዕውቅና እና ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አበረ ገለታ ተናግረዋል፡፡