አዲስ አበባ፣ 12/16/2024- የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ከቢዝነስ ተቋማት ዘላቂነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የስጋት እና የመልካም አጋጣሚ የደረጃዎች ማብራሪያ ወሳኝ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንዲሁም በሂሳብ አያያዝ እና የኦዲት ማዕቀፍ ውስጥ የሚያጋጥሙ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመፍታት ሀገራት እየሄዱበት ካለው ፍላጎት አንፃር ቦርዱ በሚያደርገው ጥረት ላይ ሐምሌ 09 ቀን 2016 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር ውይይት አካሂደ።
በዶ/ር እዮብ ተካልኝ የኢፌድሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እና የቦርዱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የተመራው ስብሰባ፣ በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች የተገኙበት ሲሆን ቦርዱ በኢትዮጵያ የአካውንታንሲ ሙያ ተቆጣጣሪ አካል እንደመሆኑ መጠን በተቋማት በሂሳብ መግለጫዎች ውስጥ እንደነኚህ አይነት መረጃዎች መካተት የተሟላ፣ አስተማማኝ እና ከአለም አቀፍ ምርጥ ልምዶች ጋር እንዲጣጣም የሚያስችሉ ርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቁመው በተጨማሪም ዶ/ር እዮብ “ከዘላቂነት ጋር የተያያዙ መረጃዎች ለኢንቨስተሮች፣ ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለህዝብ የድርጅቶችን እውነተኛ አፈፃፀምና የረጅም ጊዜ ህልውና ለመረዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ አስፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል” ብለዋል፡፡
በዕለቱም የቦርዱ የቴክኒክ አማካሪ የሆኑት አቶ ደሬጀ ገላና ከዘላቂነት ጋር የተያያዙ ስጋቶችና እድሎች ማብራሪያ ስታንዳርድን በተመለከተ የየሀገራት ተሞክሮ እስከ የትግበራ የጊዜ ሰሌዳ ያካተተ የመወያያ ፅሑፍ አቅርበዋል። የመወያያ ፅሑፉ የተለያዩ ትኩረት የሚሹ እና አካባቢያዊ፣ ማህበራዊ እና አስተዳደር (ESG) ጉዳዮችን የሚዳስሱ፣ ድርጅቶች ስለ ዘላቂነት አፈፃፀም እና ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ ተፅዕኖዎች በሂሳብ መግለጫዎቻቸው ሪፖርት እንዲያደርጉ ግልጽ እና ወጥ የሆነ ማዕቀፍ ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ተሰብሳቢዎቹ የቀረበውን የመወያያ ሃሳብ ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ጠቃሚ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ከዓለም አቀፍ የሪፖርት መስፈርቶች ጋር የማጣጣም፣ የህግ ማዕቀፍ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ቀድመው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት ለሌሎች ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ ጠንካራ ተቋማት የማፍራት ስልት፣ ጉዳዩ በዓለም ገበያ ውስጥ ለመተወን ዝቅተኛው መለኪያ እንደሆነ፣ የትግበራ ወጪው ጥቅምና ጉዳት ቢታወቅ፣ የአቅም ግንባታ እና የባለድርሻ አካላት ዝግጁነት ጉዳይ በስፋት ውይይት ተካሂደውባቸዋል፡፡
ትግበራውን በበላይነት የመምራት እና ማረጋገጫ መስጠት የቦርዱ ኃላፊነት በመሆኑ ቦርዱን ማጠናከር እና ተገቢውን ባለሙያ የሚያፈራ እና የሚያበቃ ተቋም EtICPA ማቋቋም ትኩረት የሚሻ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
“ውይይቱ ኢትዮጵያ ለዘላቂ የፋይናንስና ጤናማ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል” ያሉት የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ለዘላቂነት ሪፖርት ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የሂሳብ መግለጫዎች የበለጠ ግልፅነትን፣ ተጠያቂነትን እና ጥራትን በማረጋገጥ ጠንካራና ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩም አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ስብሰባውን ሲደመድሙ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ተግባራት ላይ ያላትን የመሪነት ሚና እና የቀጣናውን የውህደት አሳሳቢነት እውን በማድረግ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በማጉላት ተወያዮችም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካሎቻቸው ጋር ተጨማሪ ውይይት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።