The Latest from AABE

የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ ተከናወነ፡፡

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ሰራተኞች የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ክንውን እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ሐምሌ 04 ቀን 2016 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ተወያዩ፡፡

መድረኩን የመሩት የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር እንደተናገሩት ዓመታዊ ዕቅድ እና አፈጻጸሙ የአስር ዓመቱን ስትራቴጂዊ ዕቅድ እና የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድን መሰረት በማድረግ በታቀደው መሰረት መከናወኑን የስራ አመራሩ የገመገመው መሆኑን ጠቅሰው ውጤቱ መሻሻሎችን ማሳየቱን እና ለዚህም ሰራተኛው ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡

አፈፃፀሙን እና እቅዱን የስትረቴጂክ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ሕዝባዊት ተስፋዬ ያቀረቡ ሲሆን የተከናወኑ እና ያልተከናወኑ ተግባራት፣ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ከቀጣይ አቅጣጫዎች ጭምር በማብራራት የ2016 በጀት ዓመት ፊስካል አፈጻፀም 83.3 በመቶ ሆኖ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡   

በአፈፃፀሙ በተለይ ለ13 የኦዲት ደርጅቶች አዲስ የሙያ ፍቃድ የተሰጠ ሲሆን ለ219 የኦዲት ድርጅቶች እና ለ1087 የሂሳብ ድርጅቶች የእድሳት አገልግሎት መሰጠቱ፣ በ125 የሂሳብ እና የኦዲት ድርጅቶች ክትትል መደረጉ፣ 990 ሪፖርት አቅራቢ አካላት መመዝገብ መቻሉ እና የ1030 ሪፖርት አቅራቢ አካላት የፋይናንስ ሪፖርት መግለጫ መቀበሉ፣ በ24 የኦዲት ድርጅቶች በ56 የኦዲት ፋይሎች ላይ የኦዲት ጥራት ምርመራ (Audit Quality Assurance) ሥራ መከናወኑ ተብራርቷል፡፡ 66የፋይናንስ ሪፖርቶች ግምገማ ተድርጎ በተገኙ ግኝቶች ላይ ግብረ-መልስ በላኩ 64 ሪፖርት አቅራቢ አካላት ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

እንዲሁም 70 የህግ-ጥሰት ፈጽመዋል በተባሉ ባለሙያዎች እና ግለሰቦች ላይ ምርመራ የተከናወነ ሲሆን 9 ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ሥር ውለው ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ወ/ሮ ህዝባዊት አስረድተዋል፡፡

ማብራሪያውንም ተከትሎ በግዢ ሂደት ምክንያት ያልተከናወኑ ተግባራት፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች፣ የደንበኞች እና የሰራተኞች እርካታ እና ሴቶችን ለአመራርነት የማብቃት ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ 

የአፈፃፀም ግምገማው ለ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ግብዐት እንደሚሆን የጠቀሱት የቦርዱ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጽዋዬ ጥሩነህ፣ የየሥራ ክፍሎች ዕቅዶች በዝርዝር ተግባራት በመተንተን ለክትትል እና ድጋፍ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ ያስታወሱ ሲሆን ሴቶችን ለአመራርነት ማብቃት የሚለው እሳቤ ለአመራር ነት የማይበቁትን እዳያገ ልል ሁሉን ዓቀፍ ዕይታ ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡ 

በመጨረሻም ለአፈፃፀሙ መሻሻል ከቦርዱ ቁጥጥር ውጪ ከሆኑት ተግባራት በስተቀር በቅርብ ክትትል እና በሙያዊ ዲሲፕሊን የተመራ መሆኑን የጠቆሙት የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር፣ በቀጣይ የሥልጠና እና ተቋማዊ የመፈፀም አቅም፣ የደንበኛ እና የሰራተኛ እርካታ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ በቦርዱ የሪፎርም ሥራ ላይ ሁሉም ሰራተኛ እና አመራር በንቃት እና በቁርጠኝነት መሳተፍ እንዳለበት እንዲሁም ዕቅዱን ወደ ሰራተኛ በማውረድ እና በጥብቅ ዲሲፕሊን በመምራት ለስኬት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡