The Latest from AABE

ከተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ ለሃገራዊ ሉአላዊነትና ክብር በጋራ መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

የገንዘብ ሚኒስቴር “ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል መሪ ቃል ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በወጣው የማስፈፀሚያ ሰነድ ላይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት ከተውጣጡ አመራርና ሰራተኞች ጋር ሰኔ 19/2016 ዓ.ም   በሚኒስቴሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡

የውይይት መድረኩ ዋንኛ ዓላማ እንደ ሀገር ከተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሰራተኛው የችግሩን አሰከፊነት በመገንዘብ የራሱን ሚና እንዲወጣ ማስቻል ሲሆን መድረኩን በእንኳ መጧችሁ ንግግር የከፈቱት የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሬታ ሰዋሰው እንደገለጹት እኛ ኢትዮጵያዊያን ያለንን እምቅ ሃብት አቀናጅተን በመጠቀም እንደ ሀገር ከእርዳታ ጠባቂነትና ከተረጅነት መንፈስ መውጣት ይገባናል ብለዋል፡፡

በማህበረሰብ ደረጃ በችግር ጊዜ መረዳዳታችን የቆየ ሀገራዊ እሴታችን ቢሆንም አሁን እየታየ ያለውን ግላዊነት እና በእርዳታ የመኖር ልማድ አጢነንና መርምረን ዜጎች ከተረጅነት አስተሳሰብ ተላቀው ሰርተው ለመለወጥ እንዲችሉ በሚደረገው ንቅናቄ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የቀረበውን የውይይት ሰነድ ተከትሎም የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ተረጅነትና ልመና የግለሰብ፣ የማህበረሰብና የሀገርን ሁለንተናዊ ክብር ዝቅ የሚያደርግ ተግባርና አስተሳሰብ መሆኑን በመረዳት የአመለካከት ለውጥ ላይ በተደራጀ አግባብ በቅንጅት ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡