የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣
የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ “ISQM 1, ISA 315 and ISA 240” ዓለም-አቀፍ የኦዲት ሪፖርት ስታንዳርድን አስመልክቶ ለኦዲት ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎች ለሁለት ቀናት በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል ስልጠና ሰጠ፡፡
በዕለቱ የቦርዱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ አጎናፍር እንደተናገሩት የስልጠናው ዋና ዓላማ የኦዲት ባህል ግምገማን መሰረት በማድረግ የኦዲት ጥራትን በማሻሻል የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ እና እንደ ሀገር የኦዲት ሙያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሁሉም የኦዲት ድርጅቶች “ISQM 1, ISA 315 and ISA 240“የተሻሻሉ አዳዲስ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶችን መሰረት በማድረግ ጥራት ያለው የኦዲት ሪፖርት እንዲያወጡ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው በመስኩ የዳበረ ልምድ ባላቸው የውጭ ባለሙያዎች በቀጥታ በበይነ-መረብ አማካኝነት የተሰጠ ሲሆን መድረኩን ያስተባበሩት የቦርዱ የፋይናንስ ሪፖርቶች ጥራት ምርመራ አማካሪ አቶ በርናባስ ጌቱ በስልጠናው ተሳታፊዎች ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶች መተግበር ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የሚያስገኟቸውን ጠቀሜታዎች እና ቀጣይነትን አስመልክቶ እና ሌሎችም ሃሳቦች፣ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተው ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎች ተሰጥተውባቸዋል፡፡
በመጨረሻም ባለሙያዎች የኦዲት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚወጡ አዳዲስ ስታንዳርዶችን በመከታተል እና በመተግበር የህዝብ ጥቅምን ሊያስጠብቁ እንደሚገባ የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ከ120 በላይ የኦዲት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡