24

ዋነኛ መቀመጫውን በአሜሪካ በማድረግ በተለያዩ የአለማችን ሀገራት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከፍቶ የኦዲትና የፋይናንስ የምክር አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ያለውና የምስራቅ አፍሪካ የኬንያ ቅርንጫፉ PricewaterhouseCoopers (PwC) የላቀ የፋይናንስ ሪፖርት (Excellence in Financial Reporting) የአንድ ቀን ዎርክሾፕ ሀሙስ ጥር 14/2012ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀያት ሪጀንሲ ሆቴል አካሄደ።

አለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን (IFRS) መሰረት አድርጎ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሊፈጥር ስለሚችላቸው መልካም አጋጣሚዎች፣ ፈይዳዎችና  በአተገባበሩም ዙርያ ሊገጥሙ ስለሚችሉ ተግዳሮቶች ትኩረቱን በማድረግ ስልጠናው የቦርዱን ባለሙያዎች ጨምሮ በሀገሪቱ ከሚገኙ የግልና የመንግስት ባንኮችና ኢንሹራንሶች፣ ከግል ድርጅቶችና ከገንዘብ ሚኒስቴር የተውጣጡ 50 ባለሙያዎችን አካቶ ለአንድ ቀን ተካሂዷል።

ይህም በደረጃዎቹ አተገባበር ዙርያ ሪፖርት የአቅራቢ አካላት ሰልጣኝ ባለሙያዎች ዘመኑ የደረሰባቸውን የእውቀት፣ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግሮች ጥቅም ላይ በማዋል አገልግሎቶቻቸውን በጥራት ተደራሽ ለማድረግ ሚናው የላቀ ሲሆን በፋይናንስ ዘርፍ የደረጃዎች ትግበራን በበላይነት ለሚመራውና የቁጥጥር፣ የክትትልና የድጋፍ አግልግሎቶቹን እየሰጠ ለሚገኘው የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አቅሙን በማጠናከር  የተሻለና ዘመናዊ የአሰራር ስርአት ለማጎልበት እድል እንደሚፈጥር የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ በመድረኩ አስረድተዋል፡፡

PWC ከአራቱ የአለማችን ትላልቅ የኦዲት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች መካከል አንዱ መሆኑንና በዓለም ከ157 ሀገራት ላይ ከ276,000 በላይ ባለሙያዎችን ይዞ በዋነኝነት በፋይናንስ ዘርፉ ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ግለ ታሪኩ ይመሰክራል።