aabe

የኢትየጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በአለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች (IFRS First time adoption) የመጀመሪያ የትግበራ ወቅት ከሀብት ትመና እና ትርፍ ክፍፍል ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ ከኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች ማህበር ፣ ከውጪ ኦዲተሮች ማህበር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዘርፉ ምሁራን እና ከገቢዎች ሚኒስቴር ተወካዮች ከተወጣጡ 81 ተሳታፊዎች ጋር መስከረም 22 ቀን 2012ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ የግማሽ ቀን ውይይት አደረገ።

በመድረኩም የቦርዱ ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ደመላሽ ደበሌ እንደተናገሩት ከ2010 በጀት ዓመት ጀምሮ ደረጃዎቹን እየተገበሩ ያሉ ባንኮችና ኢንሹራንሶች በተለይ ከሀብት ትመና እና ትርፍ ክፍፍል ጋር ተያይዞ በትግበራው ወቅት ባጋጠሙ ክስተቶች ላይ ለመወያየት እና ወደ ተሻለ መፍትሔ ለመምጣት ያስፈለገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዕለቱም የቦርዱ የፋይናንስ ደረጃዎች ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ዘሩ ለውይይቱ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን በመነሻ ጽሁፉ መሰረትም ለሀብት ትመና ፌር ቫሊዩ ስለመጠቀምና አለመጠቀም፣የሀገሪቱን ህግጋት፣ የንግድ ህጉን፣ የታክስ ህጉንና አዋጅ 847/2006ን ባማከለ መልኩ ስለመተግበር፣ በአዋጁ የተሻሩ እና ያልተሻሩትን ለይቶ መጠቀምን በተመለከተ እና የመሳሰሉት ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

መድረኩንም የቦርዱ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት አቶ ቢርቢርሳ ደምሴ እና አቶ ስንታየሁ ደምሴ የመሩት ሲሆን የአዋጁ መውጣት የፋይናንስ ቀውስና ድርጅቶችን ከውድቀት ስጋት ለማዳን እንዲሁም የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ መቋቋምም ሙያው የህዝብን ጥቅም ማስከበሩን ማረጋገጥ እንደመሆኑ መጠን ቦርዱ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በመጋበዝ በወቅቱ መድረኩን ማዘጋጀቱ ተገቢ መሁኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም ለውይይት የቀረበው ሃሳብ የሀገሪቱን የፋይናንስ ጤናማነት ከማረጋገጥ አንጻር ጉልህ ሚና ያለውን ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብን ትግበራ እውን ለማድረግ ወሳኝና ሌሎችም ደረጃዎቹን በመተግበር ላይ የሚገኙ እና በቀጣይ የሚተገብሩ ድርጅቶች የሚከተሉት በመሆኑ የተነሱ ሃሳቦችን በማደራጀት ለዳሬከተሮች ቦርድ ለውሳኔ የሚቀርብና ቀጣይ መድረኮች ሊኖሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡