በሀገሪቱ ያሉ የግል፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የአለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች መሰረት የፋይናንስ ሪፖርታቸውን አዘጋጅተው ለቦርዱ እንዲያቀርቡ አስፈላጊውን እውቀት እንዲያሸጋግሩ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስልጠና እና የአሰልጣኞች ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዓላማውን ለማሳካት ቅድሚያ ከሰጣቸው ተግባራት አንዱ የሆነው የሙያው አፈጻጸም የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ መዋሉን ማረጋገጥ ነው፡፡

በዚሁም መሰረት ሙያውን ዓለም ከደረሰበት የጥራት ደረጃ ለማድረስና ሀገሪቱን ከሌሎች ሀገራት እኩል ተወዳዳሪ ለማድረግ በሙያው ዘርፍ ያሉ መምህራን ሚና ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ለሃያ ሰባት ለጂማ ዩኒቨርስቲ የአካውንቲንግ ክፍለ-ትምህርት መምህራን ከመስከረም 06-11/2012 ዓ.ም. በዓለም ዓቀፍ የፐብሊክ ሴክተር አካውንቲንግ ደረጃዎች (IPSAS) የአሰልጣኞች ሥልጠና መሰጠቱን የቦርዱ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ዘሩ አስታውቀዋል።

ስልጠናዎቹ ከአቶ ፈጠነ በተጨማሪ ከአቶ ታዬ ፈቃዱ የቦርዱ የሙያና ሙያተኞች ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጋር በጋራ የተሰጠ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ ለክፍለ-ትምህርቱ መምህራን በአለም አቀፉ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች ጽንሰ-ሃሳብና አተገባበር አስር ቀናት  ሰላሳ ሁለት የዘርፉ መምህራን ከሰኔ 24-ሐምሌ 03/2011 ዓ.ም. በድምሩ ለሃማሳ ዘጠኝ መምህራን ስልጠናዎቹን በመስጠት የእውቀት ሽግግር ስራ ማከናወኑን አቶ ፈጠነ አስታውሰዋል።

ዘርፉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍና ድርጅቶችን ከውድቀት ስጋት ለማዳን የሚያስችል የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓትን ተግባራዊነት ለማጠናከር የግልና የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች መምህራን ከራሳቸውም አልፎ ለቀጣይ መምህራንና ለተመራቂ ተማሪዎቻቸው ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ፣ ለአካባቢው የሪፖርት አቅራቢ አካላት አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እንዲያበረክቱ፣ በስርዓተ ትምህርት ቀረጻው በእውቀት ላይ የተደገፈ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ለሙያው ክብር የድርሻቸውን እንዲወጡ ቦርዱ እስካሁን ከዋና የመቆጣጠር ስራው ጎን ለጎን ሰላሳ ለሚሆኑ ዩኒቨርስቲዎች የዘርፉ መምህራን ሥልጠናና የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡