የኢትየጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጋር በመተባበር በዜጎች መረጃ የማግኘት መብትና በመረጃ አሰጣጥ ሂደት ላይ ለቦርዱ አመራሮች ማክሰኞ ታህሳስ 14/2012 ዓ.ም በሀርመኒ ሆቴል የግማሽ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጠ።

በእለቱም የግንዛቤ ማስጨበጫውን የሰጡት ከኢፌዲሪ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አቶ ተመስገን ኪዳኔ ሲሆኑ ዜጎች መረጃን መጠየቅ፣ማግኘት እና ማሰራጨት ዴሞክራሲያዊ መብታቸው መሆኑንና ሆኖም ከሀገር ደህንነት ጋር በተያያዘ የተከለከሉ መረጃዎች እንዳሉ፣ አመራሩም ህዝብንና መንግስትን ለአደጋ ሊያጋልጡ ከሚችሉና በህግ ከተከለከሉ መረጃዎች ውጪ ለመረጃ ጠያቂዎች በአዋጁ በተገለጸው የጊዜ ገደብ መሰረት ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በተለይ ከፋይናንስና ከንግድ ጋር በተያያዘ የሶስተኛ ወገን የንግድ መረጃዎችን ስለመጠየቅ እና ተቋማትም በምን መልኩ ማስተናገድ እንዳለባቸው መረጃዎቹን መስጠት ከሚያስከትለው አደጋ እና መከልከል የህዝብ ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር ያለውን ጠቀሜታ በማመዛዘን መወሰን እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ የቦርዱ አመራሮችም በርከት ያሉ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን አዋጁ ክፍተቶች ያሉበትና ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት ማሻሻያም ሊደረግበት በውይይት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

በግንዛቤ ማስጨበጫውም ሁሉም የቦርዱ የሥራ ሓላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን ሙያው የህዝብን ጥቅም ማስጠበቁን ማረጋገጥ አንዱ ዓላማው ለሆነው የቦርዱ አመራሮች መድረኩ መዘጋጀቱ የህዝብ ጥቅምን ለማስጠበቅ፣ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለተሳለጠ የመረጃ አሰጣጥ ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ ተጨማሪ አቅም የሰጣቸውና ለአፈጻጸሙ የበኩላቸውን እንዲወጡ እንደሚረዳ ተናግረዋል።