The Latest from AABE

የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 05 2018 .የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የ2018 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ውይይት ሁሉም የቦርዱ ሠራተኞች እና አመራሮች በተገኙበት በቦርዱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄደ፡፡

የክንውን ሪፖርቱ በቦርዱ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ በአቶ ተሾመ ደሳለኝ ቀርቦ ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገበት ሲሆን አፈፃጸሙ በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ ፣ያልተከናወኑ ተግባራት እና ያልተከናወኑበት ምክንያት ፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በማካተት የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በውይይቱም የቦርዱ ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር አፈፃፀሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት እና ከበጀት ዓመቱ ዕቅድ አንፃር አመርቂ ውጤት የተመዘገበበት ቢሆንም ብዙ መሻሻሎችን የሚጠይቁ ተግባራት መኖራቸውንም አውስተዋል፡፡ በተለይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግስታዊ  እና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በተሰራው የተቀናጀ ሥራ በርካታ ሪፖርት አቅራቢ አካላት የሂሳብ መግለጫዎቻቸውን በሚገቧቸው ደረጃዎች መሰረት አዘጋጅተው እና ኦዲት አስደርገው ወደቦርዱ ያቀረቡ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የፋይናንሺያል ሪፖርት ጥራትና የኦዲት ጥራት ማረጋገጥ ግምገማ ስራው ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መልኩ እየተከናወነ የሚገኝ መሆኑን እና በጥራት ግምገማ ሥራው የህግ ጥሰት በፈፀሙ የሒሣብ እና ኦዲት ባለሙያዎች እና ሪፖርት አቅራቢ አካላት አስተማሪ የሆኑ ህጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በቀጣይም በተሻለ መልኩ መስራትና የግምገማ ውጤቱን ለህዝብ ግልጽ ማድረግ ላይ ተኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አክለውም አጠቃላይ አፈጻጸማቸው ከመቶ ፐርሰንት በታች የሆኑ ተግባራትን ለቅሞ በመለየት ለቀጣይ ሙሉ በሙሉ መፈጸም እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ በተያያዘም ሠራተኞች በሲቪል ሰርቪሱ ሪፎርም መሠረት ለሚካሄደው የምዘና እና የማብቃት ሂደት ራሳቸውን በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ከሠራተኞች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከመድረኩ ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ    የተሰጠበት ሲሆን የቦርዱ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጽዋዬ ሙሉነህ በበኩላቸው ቅንጅታዊ አሠራርን ከተቋም ግንባታ ጋር ማስተሳሰር እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና ባለጉዳዮችን በተገቢው መንገድ ማገልገል እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡