The Latest from AABE

ETICPA, የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ ሙያ ትንሣዔ ይሆናል

ለመላው የክርስትና እምነት ተካታዮች የመስሪያ ቤታችን ሠራተኞች፣ ባለሙያዎች፣ አጋሮች እና የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ፡

በቅድሚያ እንኳን ለጌታችን እና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳዔ በዓል መታሰቢያ በሠላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡

ለክርስትና እምነት ተከታዮች ትንሳዔ፣ ዕረፍት ነው፣ የዘለዓለም ህይወትም ተስፋ ነው፡፡

በብሉይ ዘመን እግዚአብሔር “ያገልገለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ” ብሎ በሙሴ በኩል ፈርዖንን ቢጠይቀውም ፈርዖን እስራዔላዊያንን ለመልቀቅ ልቡን ሲያደነድን እግዚአብሔር ከተደጋጋሚ ርህራሔ የተሞላበት የቁጣ መቅሰፍት በኋላ በአሥረኛው የእግዚአብሔር ውሳኔ፣ ፈርዖን በልበ-ደንዳናነቱ ቢቀጥልም እያንዳንዱ እስራዔላዊ አባወራ ሁሉ የበግ ጠቦት ሰውቶ በበሩ መቃን እና ጉበን ደሙን ቢቀባ የሞት መልዐክ እንደማይነካው እና የበጉ ደም የሌለበት ቤት ግን በኩር የሆነ ሁሉ የሚቀሰፍበትን የመጨረሻውን መቅሰፍት ወደ ግብፅ ምድር ላከ፣ ፈርዖን እልኸኛነቱን ትቶ እስራዔላዊያን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡበት እና እግዚአብሔር ቀድሞ እንደተናገረው ወደተስፋይቱ ምድር የገቡበት ትልቁ የፋሲካ ሚስጥር የታየበት ነው፡፡

በዚህም መሰረት ዓመቱን ሙሉ ለሰሩት ኃጢአት ስርየት እና ነፃ የወጡበትን ቀን ለማስታወስ ለዘመናት በየዓመቱ በግ ይሰዉ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን የእግዚአብሔር ዓላማ ሰው እግዚአብሔርን በእግዚአብሔርነቱ አውቆ እንዲያመልከው እና እንዲያገለግለው እንጂ የበግ ደም ላይ ስላልነበረ ሰውም ከተደጋጋሚ ኃጢአቱ መመለስ ስላልቻለ፣ የበግ ደምም የየዓመት ኃጢአቱን እንጂ ዘለዓለማዊ ኃጢአቱን ሊያስወግድ ስላልቻለ ለአንዴ እና ለመጨረሻ አንድያ ልጁን፣ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእናታችን በብፅዕት፣ ቅድስት ድንግል ማርያም በኩል ወደ እኛ መላክ ግድ ሆነበት፡፡ ኢየሱስም በምድር ላይ የእግዚአብሔርን ዓላማ እንዳያሳካ ከሕፃንቱ ጀምሮ ብዙ እንቅፋቶች ቢደረደሩም የእግዚአብሔርን ዓላማ ማንም ሊያስቀር ስለማይችል በተወሰነለት ጊዜ ደሙን አፍስሶ፣ በቀራንዮ መስቀል “ተፈፀመ” ብሎ ወደ መቃብር ወረደ፤ በሶስተኛውም ቀን ከሙታን ተነሳ፤ ወደ ሰማይም አረገ፤ ተመልሶም ሊወስደን እንደገና በክብር ይመለሳል፤ ተስፋችንም እሱ ነው፡፡

የተከበራችሁ የመሥሪያ ቤታችን ባልደረቦች፣ አጋሮች፣ ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ ህዝቦች፣

የአካውንተንሲ ሙያ በሰው ልጅ ታሪክ ከ7000 ዓመታት በፊት በጥንታዊት ሜሴፖታሚያ ለቤተ-መቅደስ ንብረት ቆጠራ እና የቁጥጥር ሥራ እንደተጀመረ እና በሀገራችንም የሂሳብ አያያዝ መነሻው በ3ኛው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ ሃብትን እና የመንግስት ተግባራትን ለማስተዳደር መሰረታዊ የመዝገብ አያያዝ ስራዎች ይኖሩበት ከነበረው ከአክሱም መንግስት ይሁን እንጂ መደበኛ እና ስልታዊ የሂሳብ አያያዝ አሰራሮች እስከ ዘመናዊው ዘመን ድረስ እንዳልታዩ ታሪክ ያወሳናል፡፡ 
 
በ1905 እኤአ ገደማ የግብፅ ባንክ ቅርንጫፍ በሆነው የአቢሲኒያ ባንክ የተጀመረው ዘመናዊው የሂሳብ አያያዝ ሙያ በሚፈራረቁ ሥርዓቶች ውስጥ ብዙ ሂደቶችን አሳልፎ ዘመናችን ላይ ደርሷል፡፡         

የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ግን ዓለምዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሂሳብ አያያዝ ሙያ በህግ እስከተደነገገበት ጊዜ ድረስ ምንም ያክል ኢትዮጵያ የራሷ የሚባል ብሔራዊ የሒሳብ አያያዝ ደረጃ እና ተገቢው የቁጥጥር ሥርዓት ልምምዱ ባይኖራትም እንደነገሩ የህግ አካል አድርጋ በአዋጅ 847/2006 ከመቀበልም አልፎ ለተፈፃሚነቱ የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ የሚባል ተቈጣጣሪ የመንግስት መስሪያ ቤት እና የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት የሚባል ተቋም እንደሚቋቋም ተደንግጓል፡፡ በተመሳሳይም ቦርዱን ለማቋቋም እና አሰራሩን ለመወሰን በወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 332/2007 ደግሞ ወደሙያው መሰማራት ያለባቸው ቦርዱ የሚያወጣውን መስፈርት የሚያሟሉ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች እንደሚሆኑ በደንቡ አንቀፅ 6 ንዑስ አንቀፅ 1እና 10፣ አንቀፅ 17 እና 18 በስፋት ተጠቅሷል፡፡

ይሁን እንጂ በአዋጁ በተገባው ቃል መሰረት ኢትዮጵያ ባለሙያ የሚያፈራላት ኢንስቲትዩት ያልነበራት በመሆኑ በተለምዶ ይሰራበት በነበረው መስፈርት እና በገበያው ውስጥ ለነበሩት በየዓመቱ ፍቃዳቸውን በማሳደስ ብቻ ማስቀጠል ሆኗል፡፡

ይህም ለአፍሪካ እና ለመላው ዓለም ጭቁን ህዝብ ከባርነት ነፃ መውጣት ተምሳሌት ለሆነች ሀገር ስም እና ክብር የማይመጥን፣ ዓለም የደረሰበትን እና የገበያውን ፍላጎት የማይመልስ፣ በአዋጅ እና በደንብ ብቻ መደገፉ በቂ ስለማይሆን ኢንስቲትዩቱ እንዲቋቋም የውስጥ እና የውጪ አቅምን አሟጦ መጠቀምን የግድ ብሏል፡፡

ያም ሆኖ እንዳይሳካ ምንጩ ከየት የማይባሉ ሳንካዎች በዝተውበት ዓመታትን አስቆጥሮ እንዳይታሰብ የተቀበረ እስኪመስል አንዳንዶችን ተስፋ ማስቆረጡ አልቀረም፤ ግን ቢዘገይም የተቆረጠውን ቀን ማንም ማስቆም ባለመቻሉ በጊዜው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከዛም ሂደቱን ጨርሶ ለኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ ሙያ ትንሣዔ ይሆን ዘንድ በወርሃ መጋቢት ወር 2017 ዓ.ም. በኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1372/2017 ሆኖ ፀድቋል። መልካም የትንሣዔ በዓል ይሁንላችሁ፡፡

ደግሞም በቅርቡ ሥራ ሊጀምር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹ ተጠናቀዋል፤ የጊዜያዊ አስተዳደር ምክር ቤቱ ዕጩ አባላት በኢፌድሪ የገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ይፋ ይደረጋል የሚል ተስፋችን ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ትልቅ አሻራቸውን ላኖሩ፣ የቦርዱ የቀድሞም ይሁን አሁን ላሉ የቦርዱ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ አጋር እና ተባባሪ አካላት፣ ተስፋ ሣይቆርጡ በተስፋ እየተጠባበቁ ለነበሩ እና ላሉ ባለሙያዎች በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ወዳጆች ሁሉ መልካም የትንሣዔ በዓል ይሁንላችሁ፡፡

አቶ ፍቃዱ አጎናፍር

ተ/ዋና ዳይሬክተር