The Latest from AABE

ETICPA, “አዲስ ዘመን ለኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ ሙያ እና ኢኮኖሚ እድገት”

ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ህዝብ ከ600 የማይበልጡ ፕሮፌሽናል አካውንታንቶች፣ ከዚህ ውስጥ ከ150 የማይበልጡ የውጪ ኦዲተሮች እና ሁለት ሺህ የማይሞሉ በሙያው ዓለም አንቱ የተባሉ፣ ልምድ እና አቅም ያዳበሩ የተፈቀደላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ያሏት ሀገር ናት፡፡ ይህ ቁጥር በየትኛውም የምድራችን ሀገራት ከፍላጎት እና አቅርቦት አንፃር ለምጥጥን የማይቀርብ አሳሳቢ ቁጥር መሆኑ በሀገሪቱ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ እና ኦዲት ጥራት ላይም የጎላ ጉዳት ቢያስከትል ላይገርም ይችላል።

የአካውንተንሲ ሙያ በኢትዮጵያ ብዙ ሊሰራበት የሚገባ ጉድለቶች የነበሩበት መሆኑን የROSC 2017 Addis Ababa ጥናት የሚያመላክት ሲሆን አዋጅ 847/2006 የመደንገጉ እና አዋጁን ለማስፈፀም የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ እንደ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት እና የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ደግሞ በሙያዊ ሥነ-ምግባር የታነፁ ባለሙያዎችን በማፍራት እና በማብቃት ዓለም ዓቀፍ የሂሳብ እና ኦዲት ስታንዳርዶችን መሰረት በማድረግ ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርቶችን በማዘጋጀት በሀገሪቱ ጤናማ የኢኮኖሚ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ ትርጉም ያለው ሚና እንዲወጡ ትልቅ ተልዕኮ ተጥሎባቸዋል፡፡

ሆኖም ጠንካራና የተደራጀ የፕሮፌሽናል አካውንታንት ኢንስቲትዩት ሳይኖር ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት ብቻውን መፈጠሩ ከፈረሱ ጋሪውን ሳያስቀድም እንዳልቀረ ያስጠረጥራል፡፡ ሆኖም ቀድሞ የተፈጠረው ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት ተልዕኮውን ለማሳካት የቦዘነበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ግን ማሳካት የሚችለው በህግ ሊወጣው የሚገባውን ብቻ ሲሆን ምንም ያክል አንዱ የአንደኛውን ሚና ሊተካ ባይችልም በተለይ ሙያውን በማስተዋወቅ፣ በማስተማር እና በማዘጋጀት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ለኢንስቲትዩቱ መቋቋምም የተጋውን ያክል ተሳክቶለት አሁን እውን ሆኗል፡፡በአዋጁ የተጠቀሰው ኢንስቲትዩት ብቁ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎችን ማፍራት እና ሙያዊ ብቃታቸውን ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ፣ ቀጣይነት ባለው ስልጠና ሙያዊ አቅም ማጎልበት፣ አዳዲስ በሚወጡ እና የሚሻሻሉ የዘርፉ ስታንዳርዶችን እየተከታተለ ግንዛቤ የማስጨበጥ እና ለስራ ብቁ ማድረግ ይጠበቁበታል፡፡ ያለ ጠንካራ ኢንስቲትዩት፣ የሂሳብ ባለሙያዎችን ለቀጣይ ሙያዊ እድገት ማጨት፣ ክህሎትን ለማሻሻል እና ጊዜውን የሚመጥን አለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን የማግኘት እድሎች ያነሱ ናቸው።

አገር በቀል የዘርፉ ማህበራት እንደማናቸውም የሙያ ማህበራት የአባሎቻቸውን መብት እና ጥቅም እንዲሁም ሙያውን ለማጎልበት ተደራጅተው ሀገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ቢሆንም የዓለም ዓቀፉ የሂሳብ ባለሙዎች ኮንፌዴሬሽን መስፈርትን ለማሟላት የወሰደው ጊዜ ሌላው ጫና መሆኑ የሚታበል አይደለም፡፡ በበቂ፣ ብቁ እና ዓለምዓቀፍ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል የሀገሪቱን ገበያ ፍላጎት በውጤታማነት አሟልቶ ሌሎችን ማስተናገድ የሚችል አቅም ያስፈልጋል፡፡

ሙያው ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቁን ለማረጋገጥ ባለሙያው በሙያዊ ሥነ-ምግባር መታነፅ፣የሙያ ማህበራቱ የአባሎቻቸውን መብት እና ጥቅም ማስከበር እና ለሙያው ዕድገት ብሎም በሙያው ላይ የሚያንዣብቡ ማናቸውንም አደጋዎች ለመመከት ብቁ ሆነው መገኘት፣ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተፈላጊውን ድጋፍ የማግኘት እና ለሀገራዊ የጋራ ዓላማ በቅንጅት በመስራት ሃላፊነታቸውን በጋራ መወጣትን አንግበው እየታገሉ ኖረዋል ሚናቸውም ግዴታቸውም ነው፡፡

ሙያው ውስብስብ እና ተለዋዋጭ የሂሳብ ደረጃዎችን፣ የቁጥጥር መስፈርቶችን እና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ወደ ላቀ ደረጃ እያደገ የሚገኝ ሲሆን ባለሙያው እግር በእግር በመከተል ተወዳዳሪነቱን ማረጋገጥ፣ ከተለምዷዊ አሰራር እየተላቀቀ እና ከዓለም እየተቀላቀለ አዳዲስ ክህሎቶችን እየቀመረ የሀገር ኩራትነቱን ማስመስከር ይጠበቅበታል፡፡ ይህ በግል ጥረት ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር በባለቤትነት ተቀብሎ የህግ አካል አድርጎ የሚያስፈጽም አካል ያስፈልጋል፡፡ የETICPA መቋቋም ዋና ዓላማም ለዚሁ ነው፡፡ ሙያው ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቁን እና የህዝብ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጡን ለመቆጣጠርም AABE የአንበሳውን ሚና በመወጣት ከኢንስቲትዩቱ ጎን ይቆማል፡፡